Wednesday, April 29, 2020

#Ethiopia

ለህገመንግስታዊ ቀውሱ ፖሊቲካዊ እንጂ ህገዊ መፍትሄ የለም
(Translation by Moges Zewdu Teshome)
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ነሃሴ መጨረሻ ላይ ሊያደርገው ያቀደውን ምርጫ በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ማካሄድ እንደማይችል አሳውቋል። እንደ ህገመንግስቱ ድንጋጌ ደግሞ አሁን ያለው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የስራ ዘመን ከመስከረም 30 በኋላ ያበቃል ( እንዲያም ሰኔ 30 መሁን ነበረበት)። ይህም ማለት የፌደራል ፓርላማና የክክል ምክር ቤቶች የስራ ዘመን ስለሚያበቃ ይበተናሉ ማለት ነው። በፓርላማና ክልል ምክር ቤቶች የተቋቋሙት ስራ አስፈፃሚዎች የስራ ዘመንም አብሮ ያበቃል። በዚህ ሳቢያ ሁለት ጥያቄዎች ተነስተዋል። የመጀመሪያው የምርጫ ግዜ ሰሌዳን ማራዘም ይቻላል ወይ? ቢቻልስ ምርጫን ለማራዘም ስልጣን ያለው ማነው? ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ ምርጫው እስኪደርግ ድረስ መንግሥት በማን ይመራል? የሚለው ነው። ለነኚ ጥያቄዎች መንግስት አራት የመፍትሔ ሀሳቦችን አቅርቧል:-
1. በህግ መንግስት አንቀጽ 60 ስር በተደነገገው መሰረት ፓርላማውን መበተን: ይሄ ድንጋጌ በግልጽ እንዳስቀመጠው በፓርላማ ውስጥ ስምምነት ከጠፋ ወይም ጥምር ፓርቲዎች ተስማምተው መስራት ሲያቅታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማውን በመበተን በ6 ወራት ግዜ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ይደረጋል ይላል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ማድረግ የሚችለው በተቀመጠለት የ5 ዓመት ግዜ ገደብ ውስጥ ነው። ይሄም የሚያስረዳን አንቀፅ 60 የተቀመጠው የምርጫ እድሜን ለማሳጠር እንጂ ለማርዘም አይደለም። ስለዚህ ይሄኛው አማራጭ አያስኬድም።
2. የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ደንግጎ ሀገር ማስተዳደር: በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ስር በተደነገገው መሠረት ሀገር ሲወረር፣ ከመደበኛ ቁጥጥር ውጪ የወጣ የሰላም መደፍረስ ሲያጋጥም ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም የሚንስቴሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በመደንገግ ሀመንግስቱን በጊዚያዊ ሁኔታ በማገድ ሀገርን ማስተዳደር(የገጠመውን ሁኔታ ቁጥጥር ስር ማዋል) ይችላል። ይሄም ምርጫን ለማራዘም መፍትሄ አይሆንም። ሲጀመር የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ለማራዘም ኮረና ከመስከረም በኋላም መቀጠል አለበት። ሁለተኛው ደግሞ የኮረና ወረርሽኙ ቢቀጥል እንኳ የመንግስት የስልጣን ዘመን ከማብቃት አያድነውም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢራዘም እንኳን አሁን ያለው መንግስት መስከረም 30 ካበቃለት በኋል የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን የሚያስፈፅም አዲስ አካል ይቋቋማል ወይም ይመደባል እንጂ አሁን ያለው ስራ አስፈጻሚ አይቀጥልም።
3. ህገመንግስቱን ማሻሻል: ይሄም የሚሆነው የመንግስት የስራ ዘመን 5 አመት ነው ብሎ የደነገገውን አንቀጽ 54 በማሻሻል የምርጫ ግዜን ማራዘም ይቻላል የሚል ነው። ይሄን አንቀጽ ለማሻሻል የሚያፈልገው የፓርላማውንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2/3ኛ ድምፅ ማግኘት እንዲሁም ቢያንስ ከ 9ኙ ክሎች የ6ን ክልል ምክር ቤቶች አብላጫ ድምፅ ድጋፍ ማግኘት ነው። እንደሚታወቀው የፌዴራሉም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች በተጭበረበረ ምርጫ 100% በአንድ ፓርቲ ነው የተያዙት። እነኚ ምክር ቤቶች ይወስኑ ማለት ሀገራዊ ውሳኔ ሳይሆን አንድ ፓርቲ ብቻውን የስልጣን እድሜውን ማራዘም ነው። በርካታ አንባገነን መሪዎች በዓለም ላይ እንደተስተዋለው በዚህ መልክ ህግመንስትን እያሻሻሉ ነው የስልጣን ዘመናቸውን ሲያራዝሙ የቆዩት። አሁን 27 ዓመታት ሙሉ ይህችን ሀገር በጉልበት ረግጦ ሲገዛ ከቆየ አንባገነናዊ ስርዓት ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር እንድል ይሰጠል ተበሎ በሚጠበቅ ምርጫ ገዢው ፓርቲ ብቻውን እድሜውን አራዝሞ እንዲቀጥል መፍቀድ ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር ያለውን እድል ማጫናገፍ ነው።
4. የህገመንግስት ትርጓሜ መሻት: እንደሚታወቀው ህገመንግስት የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ህገመንግስቱ ስለ ምርጫ ማራዘም የደነገገው ምንም ነገር ስለሌለ ትርጉም ያስፈልገዋል የሚል ነው። ይሄም አማራጭ አያስኬድም። በመጀመሪያ ደረጃ ትርጉም የሚያስፈልገው የተፃፈ ህግ እንጂ ያልተፃፈ ህግ ትርጉም አያስፈልገውም። ሁለተኛ ህገመንግስቱ ምርጫን ስለማራዘም ያልደነገገበት ምክንያት አለው። ምርጫ እንዲረዝም ህገመንግስቱ ያልፈቀደበት ዋናው አላማ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ፓርቲዎችን አንዳሻቸው የስልጣን እንድሜያቸውን እንዳያራዝሙ ነው። 3ኛው ደግሞ የህገመንግስት ትርጉም ይደረግ ቢባል እንኳን አንድ ፓርቲ ብቻውን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጠቅልሎ ስለያዘ ( አሁን ህወሀት ብትቀነስም በጣም ትንሽ ድምጽ ነው ያላት) ይሄ አካሄድ ተቀባይነት የለውም። የምርጫ ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ውሳኔ ሳይሆን ሁሉንም ፓርቲዎች የሚመለከት ስለሁነ ገዢው ፓርቲ ብቻውን በተቆጣጠራቸው ተቋማት የሚወሰን ውስኔ ምርጫውን ከአሁኑ የማጭበርበር ያክል ነው።
ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች አሁን የደረሰውን የህገመንግስት ቀውስ (constitutional crisis) በህግ የተቀመጠ መፍትሄ የለውም። የሚኖረው ብቸኛ መፍትሔ ከፓርቲዎች የጋራ ስምምነት የሚመነጭ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ያለው የትኛውም አካሄድ ከመስከረም 30 በኋላ የመንግስት ክፍተት ( vacuum) የሚፈጥር ነው። ገዢው ፓርት በማናለኝበት ማርጫ እና አስተዳደራዊ ጊዜውን የሚያረዝም ከሆነ አሁን የተከሰተው ሀገመንግስታዊ ቀስት ወደ ፖሊቲካዊ ቀውስ ሊያድግ ይችላል። ፖሊቲካው መፍትሄ ስንል ምን ማለት ነው? በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ።

No comments: