Thursday, May 7, 2015

ጂቱ ለሚ:- "ከኦነግ ጀርባ የኦሮሞ ሕዝብ አለ!" | ሊሸሽጉት ያልተቻለ እዉነታ!


በጂቱ ለሚ* | April 2015
ሰዉዬዉ ቁጭ ብለው ሌሊት-ሌሊት ያሰባሰቧቸዉን የፈጣን ሎተሪ ቲኬታቸዉን እየቀያየሩ ሲፍቁ፣ ሲያስፍቁና ከሎተሪ መዉጫዉ ጋር ሲያመሳክሩ ያድሩ ነበር አሉ። እናማ አንደኛዉን ሲሞክሩት ውጤቱ ሌላ ነዉ። በሌላኛዉ ቢመኩም የባሰበት ሆነ! ሌላም ቢተካ ተስፋ ዬለውም። ላይተዉት ነገር የቤቱ ምሰሶና ማገሩ ‘በፈጣን ሎተሪዎቹ’ ተስፋ ላይ የተዋቀሩ ናቸዉ። አንዱ ሲጣል በሌላዉ ሲተካ ዉጤቱ እየራቀ ተስፈዉም እየመነመነ ቤቱ አልጸና ብሏቸዉ ላይ-ታቹን ሲኳትኑ በእልህ የመጨረሻ ዕድል ለመሞከር ባሕር ማዶ ድረስ ተሻግረዉ ታላቁን ‘ቶምቦላ’ በዉድ ዋጋ ይጋዛሉ። ዕድሉ ቀንቶኣቸው እነዚያን ‘ፈጣንና ፈጣጣ’ ሎተሪዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ አራግፈዉ ለመገላገል ተመኙ። ግን ክፉ ዕድል ሆኖ ብዙ የደከሙለትን ‘ቶምቦላ’ መጨረሻዉን ለማየት ሳይታደሉ የመሄጃ ጊዜያቸዉ ደረሰና የያዙትን ሁሉ ለዘመድ አዝማዶቻቸዉ በዉርስ ሰጥተዉ ይሰናበታሉ።
የሰዉዬዉ ወራሾችም የነገሩን አያያዝ አልቻሉበትምና አንዱን ሲይዙ ሌላዉ እየሸሸ ገና ከጅምሩ በሰዶ- ማሳደድ ጨዋታ ልባቸዉ ዉልቅ ይላል። “ልፋ ያለዉ በህልሙ ዳዉላ ይሸከማል” ይባል የል! ዉድ ዋጋ የተከፈለበትና እጅግ የተደከመበት ታላቁ ሎተሪም ገና ተፍቆ ሳይፈተሽ ዉጤቱ ከወዲሁ ባለማማሩ ከመጠቅለያዉ እንኳ በወጉ ሳይገለጥ እንደተሸፋፈነ ወደመጣበት መልሰዉታል። ፈጣኖቹም ቢሆኑ ኣንድ በኣንድ እየተመዘዙ ሲፋቁና ሲጣሉ የተቀሩት ደግሞ አንዳችም ተስፋ የሚጣልባቸዉ ባለመሆናቸው የሰዉዬዉ ቤት ግድግዳዉ ተንዶ ጣራዉ ሊፈራርስ የቀናት ዕድሜ ቀርተዉታል።
ጎበዝ! በዚህ ወቅት ብርቱ ጉዳዮች ኣሉብን። ለሕዝባቸዉ ነጻነትና ክብር የወደቁ ጀግኖቻችንን እናስባለን። የተያያዝነዉን ትግል ለማፋጠን ደግሞ ራሳችንን የበለጠ እናዘጋጃለን። ስለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ሲሰሙ የሚያምማቸዉን ደግሞ ጠንካራ ዉጋት እየለቀቅን የባሳ እናቃዣቸዋለን። ስለዚህም በፍጥነት ወደ ጉዳዬ ልዝለቅ!
አንድ ሕዝብ ነጻነት ከሌለዉ ህሊዉናዉ አደጋ ላይ ይወድቃል። ይህ መሰል ኣደጋ የተጋረጠበት ሕዝብ ራሱን ከመከላከል የቀደመ አሳሳቢ ጉዳይ አይኖረዉም። ለዚህም ነዉ የዚህ ዓይነቱን አደጋ መከላከል ዉዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር የሚሆነዉ። ለዚህ ዓይነቱ ግዴታ ሕዝቡ የጋራ ኃላፊነት ይኖረዋል። ይህን ሃላፊነት ለመወጣት መሪዎችንና አመራሮችን በየደራጃዉ ይሰይማል። የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ይነድፋል። ኣዋጭ የሆኑ የትግል ስልቶችን ይቀይሳል። አሳታፊና ዉጤታማ የትግል መዋቅሮችን ይዘረጋል። ኃይሉንና ጉልበቱን ያቀናጃል። ነጻነት ያለመስዋዕትነት በነጻ ኣይገኝምና ትግሉ የሚጠይቀዉን መስዋዕት ሁሉ ያቀርባል። ይህ በሕዝቡ ፍላጎትና ዉሳኔ ብቻ የሚሆን እንጂ ከየትኛዉም ኃይል ፍላጎትና ተጽዕኖ አንጻር የሚመዘንና የሚመጠን አይደለም። እንደዚያ ሊሆንም አይችልም።
ይህ አብዛኛዉ የዓለማችን ሃገራት ነጻነታቸዉን ፍለጋ ያለፉበት ጎዳና ስለሆነ የኦሮሞ ሕዝብም ነጻነቱን ለመጎናጸፍ ሊያልፍበት በሂደት ያለ ነዉ። መሪ ድርጅት አለዉ። ግልጽና ቀጥተኛ የፖለቲካ ፕሮግራምን ይከተላል። ለሠላም ቅድሚያ ይሰጣል። ሠላምን ከሚጋፉ፣ በጦርና ጦርነት ብቻ መብቱን እየረገጡ መቀጠል ለሚሹም ተገቢ ምላሽ ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ለሕዝባቸዉ ክብር ዉድ ሕይወታቸውን ለመስጠት የተዘጋጀ ሕዝባዊ ኃይል ኣለው። የሕዝባዊ ኃይል ጫና ያስጨንቃል። ጭንቀቱ ወጥሮ ሲይዝ ደግሞ ያስለፈልፋል። የሕወሃት ሰዎች ይህንን በሚገባ አይተዉታል። ጭንቀቱ ሳት ያረጋቸዉና አንዳንዴም በምጸት አንዳንዴ ደግሞ በግላጭ ከኦነግ ጀርባ የኦሮሞ ሕዝብ እንዳለ እቅጩን ይነግሩናል።
እርግጥ ነዉ! የኦሮሞ ሕዝብ ከመሪ ድርጅቱ ኦነግ ጋር ነዉ። ለእዉነቱ ማረጋገጫ የግድ የጠላት መስካሪ አያሻም። ሆኖም ግን ጠላት እንደዚያ እየመረረዉ እዉነቱን ለመቀበል ሲገደድ መስማቱ እዉነት መቼም ቢሆን እንደምታሸንፍ ማሳያ ይሆናል። በበራቸዉ ደጃፍ ያቆሙአቸዉን ምልምል አሽከሮቻቸዉን እንኳ ማመን ተስኖአቸዉ በወጡና በገቡ ቁጥር ዐይን ዐይናቸዉን እያዩ “… እነ እንቶኔ ሲፋቁ ኦነግ ይሆናሉ …!” ሲሉ እዉነቱን ኣልሳቱም። ይብዛም ይነስም በእያንዳንዱ ኦሮሞ ልብ ዉስጥ ኦነግ ተተክሏልና።
መልካም! በሂደት ሲስሟሽሹ በቀላሉ ይጨፈለቃሉና ጫን ጫን እያልናቸዉ ማስተንፈሱን እንቀጥልበት። “… ከኦነግ መፈክር ዙሪያ የኦሮሞ ሕዝብ አለ …!” ሲሉን ለቅንጣት እንኳ ብዥታ እንዳይኖረቸዉ ኦነግም ሆነ የኦነግ መፈክር ምንጩ የኦሮሞ ሕዝብ ስለመሆነ አንዱን ከሌላዉ መነጠል ፈጽሞ እንደማይቻል በድጋሚ ሙሉ መረጋገጫ እንሰጣቸዋለን። በመሠረቱ የኦሮሞ ሕዝብ የትግል አቅጣጫ የሀገር ባለቤትነቱንና ሁለንተናዊ ነጻነቱን መልሶ ማግኘት ነዉ። በሌላ አባባል የማንንም መብት ሳይጋፉ የራስን መብት ማስከበርና መጠበቅ ማለት ነዉ። እናም ታዲያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሕዝቡ የተነጠቀዉን የሀገር ባለቤትነትና ሁለንተናዊ ነጻነትን የመመለስና የመጠበቅ ግዴታ አለዉ። ለዚህም ነዉ ኦነግን ከኦሮሞ ሕዝብ ነጥሎ ለማየት የሚደረጉ ሙከራዎች ህልም እንጅ እዉን መሆን ያልተቻላቸው።
ሀሳቤን ላጠቃልል! ከዓመታት በፊት “ከዚህ ወርቅ ሕዝብ በመፈጠሬ በጣም እኮራለሁ …” ያሉን የሕወሃቱ ቁንጮ ሰዉ ለሕዝባቸዉ ያላቸዉን ፍቅርና አድናቆት በፈለጉት መልኩ የመግለጽ መብት እንዳላቸዉ መቀበል ይቻል ነበር። ሆኖም ግን አካሄዱ ለአንዱ ወርቅ ለሌላዉ ነሃስን የሚያሰጥ፣ የገዢና ተገዢ ስሜትን ለማስረጽ የተጠቀሙበት ጤናማ ያልሆነ ስልታዊ ማነጻጸሪያ መሆኑ ሲጤን ሀሳቡን በቅንነት የመቀበሉ ጉዳይ አስቸጋሪ ይሆነል። እንደዚያ ባይሆንማ ኖሮ ሌሎች ስለሕዝባቸዉ በመናገራቸዉ፣ ጭቆናንና የመከራ አገዛዝን በመቃወማቸዉና ነጻነትን በመጠየቃቸዉ በአሸባሪነት ተፈርጀው እንዲገደሉና እንዲታሰሩ ባልተደረገ ነበር። ይህ ዓይነቱ መብት ‘ለወርቃማዉ ሕዝብ’ ብቻ የተገባ እንጅ ሌሎች ሊመኙት እንኳ እንደማይገባ በተግባር አረጋግጠዉታል። ማንም የራሱን ወርቅ በአግባቡ ሊያጌጥበት ይችላል። “ወርቅነኝ …!” ብለዉ ሌላዉን ለመርገጥ መነሳት ግን ነዉር ነዉ።
እና አሁንስ ምን ቀራቸዉ? ይህን አጥርቶ ለማየት ስለሚሳናቸዉ ቀሪ ዕድላቸዉን እኛዉ ብናመላክታቸዉስ!
እንዲህ ነዉ የሚሆነዉ፥ አንድ ነፋሻማ ወረት ይመጣል። በዚያን ጊዜ እሩቅ የመሰላቸዉ እሳት በቅጽበት ይደርስና የሚመኩበትን የገለባ ክምር ይበላል። ያን ጊዜ ዓይናቸዉ ይገለጥና የተጓዙበት መንገድ ምንኛ የተሳሳተ እንደሆነ ወለል ብሎ ይታያቸዉ ይሆናል። አሁንም ባይታያቸዉ ነዉ እንጂ እሳቱም ነፋሱም በዙሪያቸው አድፍጧል – ያ እሳት ሕዝባዊ ኃይል ነዉ። ሕዝባዊ ኃይሉ ደግሞ ነዉረኛዉን ከነነዉሩ ያስወግዳል።
ድል ለኦሮሞ ሕዝብ!
ጂቱ ለሚ ነኝ

No comments: