Tuesday, August 4, 2015

22 አመት እስራት ያስፈረደብን ኢስላማዊ መንግስት ወይስ ኢስላማዊ መጅሊስ እንዲቋቋም መጠየቃችን??

አቡ ዳውድ ኡስማን
የኢትዬጲያ ህዝበ ሙስሊም በኮሚቴዎቻችን አማካኝነት ለመንግስት ያቀረብነው ጥያቄ ኢስላማዊ መጅሊስ ይመስረት እንጂ ኢስላማዊ መንግስት ይቋቋምል የሚል ጥያቄ አልነበረም፡፡ ኮሚቴዎቻችንን እስከ 22 አመት የሚደርስ እስራት ያስቀጣቸው ወንጀል ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት ህዝብን ለሽብር በማነሳሳት የሚል አሳፋሪ የሃሰት ክስ ነበር፡፡ አንዳንድ የሌላ እምነት ተከታዬች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ወይም የሚከፈላቸው ካድሬዎች ኮሚቴዎቻችን እንደተባለው ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ መንግስት ያሰራቸው እንደሆነ አስመስለው ሲያቀርቡ እና አስተያየት ሲሰጡ ታዝቤያለው፡፡
እስቲ ለማንኛውም እዚህ ጋር ቆም እንበልናል ኢስላማዊ መጅሊስ ይመስረት ማለታችን ከቶውንስ በምን ስሌት ኢስላማዊ መንግስት ለመስረት መንቀሳቀስ በሚል ሊተረጎም እንደሚችል አብረን እንመልከተው
ቅድሚያ የመጅሊስ እና የመንግስትን ልዩነት ይህን ይመስላል
1. መጅሊስ የሙስሊሞች ተቋም ሲሆን መንግስት ግን የአንድን ሃገር ህዝብ በበላይነት በምርጫ ተመርጦ የሚያስተዳደር አካል ነው፡፡
2. መጅሊስ በሙስሊሞች በሚመረጡ የሃይማኖት አባቶች የሚመራ ሲሆን መንግስት ግን በሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች ሃይማኖት፣ዘር፣ቀለም ሳይለያቸው በጋራ ያስተዳድረናል የሚሉትን በምርጫ ወስነው የሚሰርቱት አካል ነው፡፡
3. መጅሊስ በህዝበ ሙስሊሙ በየመስጂዱ በሚመረጡ የሃይማኖት አባቶች የሚመራ ሲሆን መንግስት ግን በቀበሌ ወይም በየምርጫ ጣብያ ተምርጦ በአብላጫ ድምፅ የፓርላማ ወንበር ባገኘ ፓርቲ የሚመራ አካል ነው፡፡
4. ኢስላማዊ መጅሊስ ማለት በኢትዬጲያ ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞችን ወኪል በመሆን ከየትኛውም የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ፀድቶ በሃይማኖታዊ ጉዳዬች ላይ ሙስሊሙን ወከሎ የሚሰራ፣ ሃይማኖቱን ምዕመናን የሚማሩበትን እና የሚተገብሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች፣ አማኙ ማህበረሰብ ከመንፈሳዊ ሂወቱ በተጨማሪም በሃገሪቱ ሰላም እና ልማት ላይ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያግዝ ተቋም ማለት ነው፡፡ መንግስት ማለት ግን ከሃይማኖታዊ ጉዳዬች በጸዳ መልኩ በሁሉም የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ሌሎች ተግባራቶች ላይ ሀዝብን ተጠቃሚ እንዲሆን እና ዜጎች በሃገራችን በሰላም፣በአንድነት፣በነፃነት እና በሃገራቸው ፍትሃዊ በሆነ ልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ተግባር የሚያከናውን ግዙፍ አካል ነው፡፡
5. በተጨማሪም መጅሊስ እና መንግስት አንድ አለመሆናቸውን፣አንድ ሊሆኑም እንደማይችሉ በህገመንግስቱ አንቀፅ 11 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ይህ የሰማይ እና የምድር ልዩነት እያለ ከቶውንስ እንዴት ኢስላማዊ መጅሊስ እና ኢስላማዊ መንግስትን ገዢው ፓርቲ መለየት ተሳነው??
በትግራይ ክልል የውቅሮ ከተማ ህዝበ ሙስሊም ወኪል የነበሩት ኡስታዝ ቡሽራ ያህያ ፍርድ ቤት መጅሊስን ተቃውማቹሃል በሚል በሽብር ወንጀል በተከሰሱበት ወቅት የመከላከያ ቃላቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለው ነበር
“እኛ እኮ መጅሊስ እና መንግስት የተለያዩ መስሎን ነበር፡፡ በህዝበ ሙስሊሙ ያልተመረጡ ህገ ወጥ አመራሮችን ህዝበ በመረጣቸው ይተኩ ብለን የመጅሊሱን አመራሮች መቃወማችን መንግስትን እየተቃወምን መሆኑን አላወቅንም ነበር ፡፡ መጅሊስ ማለት መንግስት መሆኑን አሁን ነው ያወቅነው” በማለት ቃላቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
በትክክልም የሙስሊሞች ተቋም የሆነው ኢስላማዊ መጅሊስ ይቋቋም ብሎ መጠየቅ ኢስላማዊ መንግስት ይመስረት ብሎ ከመጠቅ ጋር አንድ ሊሆን የሚችለው መንግስት እና መጅሊሱ አንድ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡
መንግስትም በሃምሌ 27 የፍርድ ውሳኔ በአደባባይ ያረጋገጠልን ነገር ቢኖር ይህንን ነው፡፡ የህዝበ ጥያቄ አንግበው መንግስት ጋር የቀረቡ ወኪሎችን እንዴት የመጅሊሱ አመራሮች ይቀየር ትሉኛላችሁ ? ምርጫው ቀበሌ ሳይሆን መስጂድ ውስጥ እንዴት ይካሄድ ትሉኛላቹ? ምርጫውንስ እንዴት ሙስሊሙ ነፃ ሆኖ እራሱ በሚያምንባቸው ህዝባዊ የምርጫ አስፈፃሚዎች ይካሄድ እንዴት ትላላችሁ?. መጅሊሱን መንካት እኔን መንካት ነው በመሆኑም ጥያቄያችሁ መጅሊሱን እንቀይር ማለታችሁ አንዱን የኔን ተቋም ኢስላማዊ ይሁን ማለታችሁ ነውና በማለት የ 22 አመት እስር ቅጣት በይኖባቸዋል፡፡
ሃገራችን ኢትዬጲያ ይህን ፍትህ የሚያሰፍን መሪ አልሰጣትም ፡፡ ጥቁሩን በነጭ ቀየረው.አሸባሪውን በንፁሃን መነዘረው፣ ህገ አክብሩ በሃይማኖት ጣልቃ አትግቡ ብሎ በአደባባይ ህገ መንግስቱን የሰበከውን ህገ መንግስቱን አፍራሽ ተብሎ በ22 አመት እስራት በግፍ እንዲቀጣ አደረገው፣ ሰላም የሰበከውን ሰላም አደፍራሽ አለው፣ ወዘተ…..
ሃይማኖት እና መንግስትን ለመደባለቅ የሚሞከር በፀረ ሽብር ክሱ 22 አመት እስራት የሚቀጣ ከሆነ ሐይማኖት እና መንግስት ይለያዩ፣ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ እጁን ጣልቃ አያግባ ፣የህገ መንግስቱ አንቀፅ 11 ይከበር ያለ አካልስ ምን መሸለም ይኖርበታል?? ይህ ያደረጉት ወኪሎቻችንስ አሁን እጣ ፈንታቸው ምን ሆነ??
መጅሊሱን እና መንግስትን አንድ ተቋም ያደረጋቸው፣ የሃይማኖት ተቋሙን በፖለቲካ መሪ ካድሬዎች እንዲመሩ ያደረገ፣ የእምነት ቦታዎችን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ያደረገ ባጭሩ አብዬታዊ መጅሊስ የመሰረተው አካልስ በፀር ሽብር ህጉ በስንት አመት ይቀጣ???
'አብዬታዊ መጅሊስ "በኢስላማዊ መጅሊስ ይተካ በማለታችን ነው ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት በማሴር በሚል የሃሰት ዲሪቶ ክስ የወከልናቸው ኮሚቴዎቻችን በግፍ እስራት የተበየነባቸው፡፡
አብዬታዊ መጅሊስን ወይም መንግስታዊ መጅሊስን መቃወም ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት መጣር መሆኑን ገዢዎቻችን እስቲ ከህገ መንግስቱም ሆነ ምናልባትም እነሱ ብቻ ከሚመሩበት ህግ ካላቸው በገባቸው ቋንቋ ያስረዱን??
በየትኛው የአለማችን ክፍል ይሆን የሃገሪቱ መተዳደሪያ ደንብ የሆነውን ህገ መንግስት ይከበር ብሎ የሚጠይቅ አሸባሪ ያለው??የትኛው አሸባሪ ይሆን ህግ መንግስቱን በእጁ ይዞ በአደባባይ ህጉን አክብሩ እያለ የሚሰብክ?? የትኛው አሸባሪ ይሆን ሲደበድቧችሁ፣ሲመቷቹህ፣ሲገድሏቹም በሰላማዊ መንገድ ችላቹህ ዝም በሉዋቸው የሚል አሸባሪ ያለው?? በየትኛው የአለማችን ክፍል ይሆን የሰው ሰራሽ ህግ የሆነውን ህገ መንግስት ይከበር እያለ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚንቀሳቀስ አሸባሪ ያለው?? የትኛው አሸባሪ ነው በአደባባይ የሌሎች እምነት ተከታዬችን አክብሩ፣በሰላም ተኗኗሩ እያለ የሚሰብከው??የትኛው አሸባሪ ነው በሚሊዬን የሚቆጠር ደጋፊ ኖሮት ህግ እና ስርአት አክብሮ እንዲከበር የሚንቀሳቀሰው??በየትኛው ሃገር ነው ለሃገሪቷ ልማት እና ሰላም ሁሌም የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚወጣ አሸባሪ ያለው?? የትኛው አሸባሪ ነው ሰላምን፣ ፍቅርን፣መቻቻልን፣አንድነትን የሚሰብክ ?? የዚህ መሰሉ አሸባሪ ያለው እምዬ ሃገሬ ኢትዬጲያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ይህን ተግባር በፈፀም የተወነጀሉት እነዚህ ብርቅዬ የሃገር ሃብት የሆኑ ኮሚቴዎቻችን ናቸው!!!
ውሸት ለጊዜው ፎቅ ገንብታ ብትቀመጠም በደሳሳ ጎጆ ያለችው እውነት አንድ ቀን ፈንቅላ መውጣቷ አይቀርም!
ውድ ወኪሎቻችን የሃቅ ፈራጁ ጌታ ነፃ ያወጣቹሃል ኢን ሻ አላህ
መስዋት እየሆኑ ለሚገኙት ኮሚቴዎቻን አላህ ብርታቱን፣ ቅዋውን፣ ሰብሩን፣ ኢስቲቃማውን፣ ደስታውን፣ ሰኪናውን ፣ ኢህላሱን ይወፍቃቸው!
አሚን

No comments: