Friday, May 8, 2020

#Ethiopia

ብልጽግና ወይስ መልኩን የቀየረ ጭቆና?
በ Sadik Ahmed
ህወሃት መራሹን ስርዓት ስንታገል «የባሰ አታምጣ» በሚሉት የፍርሃት ቅኝት የነበረው ቅዋሜ አይረሳም።ቅዋሜው ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ የዘለገ ነበር።የሰዎች ሐሳብን የመግለጽ የተከበረባት አሜሪካ ዜግነት የወሰዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳ ሳይቀር አገር የመግባትና የመውጣትን መብት ላለማጣት በፍርሃት መዘፈቃቸው የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።በምድረ-አሜሪካ መንገድ ላይ ሲያኑን አቅጣጫ የሚቀይ፣ስንደውልላቸው በፍርሃት የሚርዱ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ የለጠፉትን ፎቶግራፍ ላይክ ስናረግላቸው እንደ እርግማን የሚቆጥሩትን ስናስታውስ ፈገግ ከማለት ውጪ አማራጭ የለንም።
መሬት ላይ ጭቆናን ፊት ለፊት እየተጋፈጡ መስዋእትነት እየከፍሉ የሚታገሉ ጀግኖች ሚናን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሚናችንን አምብዛም የጎላ ነበር ለማለት ብንቸገርም አገር የመግባት መብትን ማጣት፣የቤተሰቦቻችን በፍርሃትና በሰቆቃ በመኖር ያሳለፉት ግዜ ግን የሚረሳ አይደለም።ህዝብ በነቂስ የተሳተፈበት ትግል ውጤት አመጣ።ህወሃት መራሹ ቡድን ጓዙን ጠቅልሎ ወደ መቀሌ አቀና።እርቅና ሰላምን ለማውረድ ተነሳሽነቱ ጎላ።የህወሃትን ሚና የቀነሰው ኢህአዴግ ተሳስቼያለሁ፣አጥፍቻለሁ፣ህዝብ ይማረኝና ተሃድሶአዊ ለውጥን አመጣለሁ እነርሱ «የቀን ጅብ ናቸው» ሲልም ተናዘዘ።
የተሰደደው ወደ አገር ገባ።እኛም እድሉን አግኝተን ለሳምንታት ያልተረጋጋች ኢትዮጵያን አይተን ተመለስን።ተስፋና ስጋት ኢትዮጵያ ውስጥ አብረው እየተጓዙ ባለበት አኳሗን ብሔራዊ መግባባትና ይቅር መባባሉ ወደ መሬት በተግባር መውረድ አልቻሉም።በሁሉም መስክ የዘር የበላይነት ለማንገስ የሚደረጉት ፍትጊያዎች ህዝብ እንዲቋሰል አደረጉትና «የባሰውን አታምጣ» የሚለው ስሌት ጎልቶ ወጣ።ተሃድሶአዊ ለውጡ ደብዝዞ መደመር ገዘፈ።ከመደመር ደግሞ «ብልጽግና» ወደ ሚሉት አዲስ ትርክት ተገባ።
ብልጽግና በ‹የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰምበሌጥ› አምስት ህጋዊ አመታትን ለመጎናጸፍ ተጣደፈ።ሌላው ቀርቶ ከበይነ-መረብ ያወረደው አዲሱ አርማ የምእራብ አገራት አብያተ-ክርስቲያናት የሚጠቀሙበት ለመሆኑ ለማገናዘብ ግድ አላለውም።የገንዘብ መዋጮው ደራ።በግዳጅ ገንዘብ አዋጡ እየተባልን ነው የሚል እሮሮ ይሰማ ጀመር።የምርጫ ቦርድ ወደ ብልጽግና ተዘንብሎ መዝረክረኩ ቀጥሎ ሳለ ኮሮና ቫይረስ መጣና ስሌቱ ዳግም ተቀየረ።
ከኢህአዴግነት ወደ ብልጽግና የተሸጋገረውን የፖለቲካ ቡድን በስልጣን ላይ ለተወሰነ ግዜ እንዲቆይ በህገ-መንግስት አተገባበር ላይ ክርክሮች እየተደረጉ ነው።ይህ መልካም ነው።ህወሃት የተቀነሰበት ኢህአዴግ ግዜው ቢያበቃም ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሁነኛ ምርጫ የማድረግ አቅም እስኪኖር ድረስ በመግባባት ላይ በተመሰረተ አግባብ በሐላፊነት እንዲቀጥል ማድረጉ ሚዛን ይደፋል ቢባል የእብለት አይሆንም።
ኢህአዴግ ሊወድቅ ሲል ተሃድሶአዊ ለውጥን ለማስፈንና ለማሻገር እድል የተሰጠው የአሁኑ ብልጽግና በጉልበትና በማስፈራራት ቀጥላለሁ ካለ የህዝብን ሰቆቃ ከማፋፋምና ህዝባዊ አመጽን ከመውለድ በስተቀር ስኬትን እንደማይጎናጸፍ ማሳሰቡም ግድ ነው።ይህ አጋጣሚ የተዘነጋውን ብሔራዊ መግባባትና እርቅ የሚተገበርበት ቢሆን ኢትዮጵያ ለወደፊት የሚገጥሟትን ፈተናዎች ታልፍ ዘንድ አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለ።
ህዝቡ ጭቆናን ለማስቀረት ታግሏል።የህይወት መስዋትነት ከፍሏል።የወጣት ሰማእታት ደም አልደረቀም።‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ ባለው የምጣኔ-ሐብት ችግር ላይ አገሪቷ ውስጥ ዘርን መሰረት ያደርገው ጥቃትም እልባት አላገኘም።መንግስት የሚያደርገው እስር ዛሬም አልተቋረጠም።ከሁለት አመታት በፊት ተነቃንቆ የነበረው ኢህአዴጋዊ አምባገነናዊት ስሙን በመቀየር መሰረቱ ማጠንከር ጀምሯል።ፈላጭ ቆራጭ በሆኑት አጼ-ሐይለስላሴ፣ኮሎኔል መንግስቱ ሐይለማሪያምና መለስ ዜናዊ የተገዛችዋ ኢትዮጵያ አሁንም የሚያሻት «ግለሰባዊ ግዝፈት ነው» የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ የትግል አጋሮቻችንን ማስተዋሉ ግር ያሰኛል።የሙሴን በትር የጨበጠ ፖለቲከኛ በዘመናችን አለ ተብሎ አይታሰብም። ልክ የሆሊውድ እውቅ ተዋኒያን ገጽታቸውን በሌሎች ላይ አስርጸው ተመላኪ እንደሚሆኑት ሁሉ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ችግሮች መፍትሔን ለጋሽ የሆነ ግለሰብ እንዳለ ለማሳየት የሚደረገው ወከባ ትውልድን አምካኝ ነው።ሰላሙንና ደህንነቱ እንዳይዛባ ለፍትህ ጥሪዎች ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› በማለት ‹እስኪያልፍ ያለፋልን› አምኖ የተቀበለው የህብረተሰባችን ክፍል ቁጥሩ ቀላል አይደለም።
የዘመናት ሰቆቃ ተቀርፎ ፍትህ የነገሰባትን ኢትዮጵያ የማየት ተስፋ ከሁለት አመት በፊት እንደ ጧት ጸሃይ ፈክቶ የነበረ ቢሆንም እኔ ልምራ፣እኔ የተሻለን አውቃለሁ፣የኔ ሐሳብ የተሻለ ነው የሚሉት ፖለቲካዊ ሽኩቻ ስጋት በመሆኑ የተስፋው ብርሃን እየደበዘዘ ነው።ህወሃት የሚባል አንድ የጋራ ጠላት የነበራቸው ታጋዮች ጣት መጠቋቆም ጀምረዋል።ያ የጋራ ጠላታቸው ትወናውን ትቶ ከመድረክ ላይ ቢወርድም በብእርስ ስሙ ደራሲ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለ።አሁን የነጻነት ታጋዮች እርስ በርሳቸው እየተናቆሩ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህን ማግኘት አለበት በማለት የታገሉ፣የታሰሩ፣የተገረፉ፣በአሸባሪነት የተፈረጁ፣የተሰደዱና የለውጥ አሻራቸውን በትግሉ ላይ ያሰፈሩ የትግል አጋሮች በተለያየ ጎራ ውስጥ በመግባት ትግሉን መልሰው እየታገሉት ነው።
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው በምድረ-አሜሪካ እኛን በአካልም ይሁን በስልክም ሰላም ለማለት የሚሰጉ፣ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ሲለጥፉ ላይክ ስናረግላቸው የሚርበተበቱ፣ባጋጣሚ ፎቶ ከኛ ጋር ተነስተው እባክህን ፎቶውን ከስልክህ ላይ ዲሊት አርግልኝ የሚሉ ዛሬ ደርሶ ታጋይ፣ዛሬ ወዶ-ገብ ካድሬ ሲሆኑ እያስተዋልን ነው።ብዙዎች ጭቆናን እየታገሉ «ድምጻችን ይሰማ» በማለት ፊት ለፊት ሲታዩ ሰባት አመት ያሉበት የማይታወቅ፤ ድምጻቸው በለሆሳስ እንኳ ያልተሰማ ዛሬ እንደገደል ማሚቱ ይጮሃሉ።ነገ የቁርጥ ቀን ሲመጣ የሚበትኑ ዛሬ ፊት ለፊት ሆነው የሚጮሁላትን ሰዎችን ኢትዮጵያ አግኝታለች።ነገ አገርን የማዳን ደወል ዳግም እስኪደውል ድረስ ሐይልን ለመቆጠብ የተገደዱ ብዙ የቁርጥ ቀን ልጆችን ኢትዮጵያ አፍርታለች።በዚህ ፈታኝ ወቅት ሚናን «በጥሞና» መፈተሹ ግድ ሆኗል።የጥሞና ግዜም ያሻል።
ለማጠቃለል ዜጎች ከ50 አመት በላይ የታገሉበትን የብሔር ትግል በ«ብልጽግና» ረጅም ገመድ እግር-ትወርች መጠፈር አይቻልም።የዜግነት ፖለቲካን የሚያቀነቅነውን «አሃዳዊ» ብሎ ማግለል አይቻልም።አዛውንት ህወሃቶችን በጡረታ እንዲቀመጡ አርጎ የትግራይ ወጣት በአገሩ ጉዳዮች ላይ በትጋት እንዲሳተፍ ማድረጉ ተገቢ ነው።ጥያቄው ሁለትና ከዚያም በላይ የሆኑ ተገዳዳሪ ሐይላትን ወደ መሐል በማምጣት እንዴት «የኔ ሐሳብ ይበለጥ» ከሚሉት ፖለቲካዊ አጣብቂኝ እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል ነው።ይህ ደግሞ አገርን ከፖለቲካዊ ጥቅም በላይ መውደድን ይጠይቃል። ብሔራዊ መግባባትን ማስፈኑ ተረስቷል።ስለዚህ ሁሉንም አመለካከት ያማከለ ውይይትን ኢትዮጵያ ከመቸውም ግዜ በላይ ትሻለች።
27 አመት የአገሩን ህዝብ የጨቆነ የጎረቤት አገሩ የኤርትራ መንግስት ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሄን አምጪ ሊሆን አይችልም።ጥሎ ማለፍና የሴራ ፖለቲካ ትውልድን ከማክሰር ውጪ ያለንበትን ዘመን አይመጥኑምና አገር ፖለቲካዊ ቤተ-ሙከራ አለመሆኗን እንወቅ።በተለይ በነጻነት ሰርቶ መኖር በሚቻልባቸው አውሮፓና አሜሪካ ያሉ የያኔ የትግል አጋሮች የአሁን የብልጽግና-ኢህአዴግ ምስለኔዎች የታገሉበትን መርህ አክባሪ ይሆኑ ዘንድ ይጠበቃል።ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆርቋሪ በመሆን የህሊና ነጻነታቸውን ከሟሟት እንዲቆጠቡም ይመከራል።ስለምን? ትግላቸውን በመታገላቸው ከተጠያቂነት አይድኑምና።
ልብ ያለው ልብ ይበል!

No comments: