ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ/ም
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ህገ-መንግስታዊ አጣብቂኝን ለመሻገር የሚረዳ የመፍትሄ አቅጣጫ
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 ጠቅላላ ምርጫን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይችል መግለጹ ይታወሳል። ይህንኑ ውሳኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቆታል። በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የመንግሥት የሥራ ዘመን አምስት (5) ዓመት ብቻ ስለሆነ አሁን ያለው መንግሥት ከመስከረም 30/2013 በኋላ ሕጋዊነቱ ያበቃል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ምርጫ ከመደረጉ በፊት የመንግሥት የሥራ ዘመን የሚያበቃ መሆኑ የሚያስከትለውን ክፍተት ለመሙላት ያስችላል ያላቸውን አራት አማራጮች መንግሥት አቅርቧል። እኛ ስማችን በዚህ መግለጫ ግርጌ የተዘረዝርን የፖለቲካ ድርጅቶች በተፈጠረው የሕገ-መንግሥት ቀውስ እና መፍትሄ ሐሳቦች ተብለው የቀረቡትን አማራጮች ገምግመን የሚከተለውን አቋም ይዘናል።
1. ሕገ-መንግሥቱ ሥልጣን በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ብቻ መያዝ እንደሚቻል፣ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መደረግ እንዳለበት፣ የመንግሥት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ አስቀምጧል። ምርጫ ቦርድ እንዳሳወቀው አሁን በሥራ ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን ከማብቃቱ በፊት ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ስለገለጸ፣ ከመስከረም 30 በኋላ ሀገርን ማሥተዳደር የሚያስችል ሕጋዊ መሰረት ሊኖረው አይችልም።
2. በእኛ በኩል ከፊት ለፊታችን የተጋረጠውን ህገ መንግስታዊ ቀውስ ለመፍታት በመንግሥት የቀረቡትን አማራጮች በሚገባ ገምግመናል። ምርጫው በህገመንግስቱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መደረግ ባለመቻሉ እና መተላለፉን ተከትሎ የቀረቡት አማራጮች አንዳቸውም የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ መከራከሪያ ማቅረብ እንዳልቻሉም ተገንዝበናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ምርጫን ማስተላለፍም ሆነ የመንግሥትን የሥራ ጊዜ ማራዘም ሕገ-መንግሥቱ አይፈቅድም፡፡ በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 60 መሰረት ፓርላማውን መበተን የሚችሉት ምርጫን ከአምስት ዓመቱ የግዜ ቀነ ገደብ አስቀድሞ ወይም አሳጥሮ ለማካሄድ እንጂ መደበኛውን የምርጫ ግዜ ለማራዘም አይደለም። ሕገ-መንግሥቱን በማሻሻል የመንግስትን የስልጣን ዘመን ማራዘምም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር መደበኛ የምርጫ ግዜ ለማራዘም የሚደረገው የህግ ማሻሻል ሂደት ውስብስብ ስራዎችን የሚጠይቅ ፤ አለመግባባቶችን የሚፈጥር እና ሰፊ የሕዝብ ውይይት ሂደት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ አሁን ባለው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ፈጽሞ አይቻልም። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ ባልነበረበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በአንድ ፓርቲ በተያዙ የፌዴራል እና የክልል ምክርቤቶች ሕገ-መንግሥቱን ለማማሻሻል መሞከርም ሆነ በህገ መንግስቱ የሌለ አንቀጽ ለመተርጎም መንቀሳቀስ የሚፈጠረውን ክፍተት ፍትሐዊ እና ቅቡልነት ባለው መልኩ ለመሙላት የሚጠቅም ሆኖ አላገኘነውም። በአንድ ፓርቲ አባለት በተያዘ ምክርቤት በህገ-መንግስቱ ያልተካተተን ጉዳይ ተርጉሞ የመንግስትን የስራ ዘመን ማራዘም ቅቡልነትን የባሰ የሚሸረሽር እንጂ የሚያጠናክር አካሄድ አይደለም።
3. እንደ አራተኛ አማራጭ የቀረበው ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሐሳብም ቢሆን መፍትሄም ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ-መንግስቱን ለመተርጎም ስልጣን ቢኖረውም በህገ-መንግሥቱ ሰፍረው ካሉት አንቀጾች ወስጥ ስልጣን ማስተላለፍንም ሆነ ምርጫን ማራዘም በሚመለከት ክርክር ያስነሱ አንቀጾች የሉም። ምርጫን ማስተላለፍንም ሆነ የመንግስት ስልጣንን ማራዘም የሚመለከት አንቀጽ ፈጽሞ በህገ-መንግስቱ ያልተካተቱ በመሆኑ ምክር ቤቱ በህገ-መንግስቱ ያልተካተቱ ጉዳዮችን መተርጎም አይችልም።
4. መፍትሔው በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ አደጋን በጋራ እየተከላከልን እና በሌላ በኩል ለምርጫ እየተዘጋጀን ወረረሽኙ አልፎ (ተወግዶ) ምርጫ እስክናካሂድ ድረስ የሚፈጠረውን የመንግስት ስልጣን ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ ሀገራዊ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መደረስ ብቻ ነው ብለን አናምናለን። የሽግግር ወቅት የፖለቲካ አደረጃጀት የሚያስፈልግ መሆኑ ቢታወቅም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን ማከናወን ቀላል እንደማይሆን እናምናለን። በመሆኑም አሁን ያለውን መንግስታዊ መዋቅር ተጠቅመን የዕለት ተዕለት የመንግስት ስራ ማከናወን አለበት ብለን እናምናለን። የፖለቲካ መፍትሄ ነው ብለን የደርስንበትን በዝርዝር የሚገልጽ ሰነድ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና የህግ አውጪው አካል ለማቅረብም ዝግጅታችንን አጠናቅቀናል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም በመንግስት በተገባው ቃል መሰረት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማወያየት ዝግጁ ናቸው ብለን በተስፋ እየተጠባበቅን ነው።
5. ከዚህ ውጪ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ ፖለቲካዊ፣ ህጋዊና እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ስለሌለው አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስና ብጥብጥ የሚወስድ ነው የሚል ስጋት አለን።
ስለሆነም ቅቡልነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚከተሉትን ወሳኝ መርሆች መከተል እንደሚኖርብን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡-
1. ውይይቱ እና ድርድሩ የ2012 ምርጫን ለመወዳደር ተመዝግበው መስፈርት ያሟሉ የፖለቲካ ድርጅቶችንና ጥምረቶችን ብቻ ያሳተፈ መሆን አለበት፣
2. ውይይቱ እና ድርድሩ ገለልተኛ በሆነ አካል መመራት አለበት
3. በድርድሩ የሚደረሰው ስምምነት በሁሉም ወገን ተፈጻሚነት ያለው ( binding) መሆን አለበት።
የመግለጫው አካል ፓርቲዎች -የትብብር ለህብረ-ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፊዴራሊዝም አባል ድርጅቶች
1.-የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
2-የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር
3.የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ
4.የአገው ብሔራዊ ሸንጎ
5. የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ
6. አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ
7. ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ
ሰላም ፣ነጻነትና ዲሞክራሲ ለሁሉም ህዝቦች