Saturday, September 5, 2020

#AbiyMustGo#Ethiopia

OMN: (September 4,2020) እኔ ምንም ዓይነት ወንጀል እንደሌለብኝ መቶ በመቶ አውቃለሁ፤ ከዚህ ቀደምም ሀሰተኛ መስካሪዎች ሀሰተኛ ስምና ማንነትነትን ተላብሰው አጠገቤ ቁጭ ብለው በሀሰት መስክረውብኝ ተፈርዶብኝ ነበር ፤ ዛሬም ያንኑን እየደገሙ ነው ሲሉ አቶ በቀለ ገርባ ለፍርድ ቤት ተናገሩ።
የአገሪቷ የፍትህ ስርዓቱ ተንኮተኩቷል፤ አቶ በቀለ ገርባ
እኔና ቤተሰቤ በአገሪቷ የፍትህ ስርዓት ክፉኛ ከተጎዱት ውስጥ አንዱ ነን፤ እኔ ደምበኛችሁ ሆኜአለሁ ያሉት በሚድያ እኛን ጭራቅ አድርጎ የማቅረብ ዘመቻ ቀጥሎበታል በማለት ተናግረዋል።
=============
በቀለ ገርባ በችሎት ከተናገራቸው:
---
ለአገራችን ይጠቅማል ብለን ያሰብነውን ሁሉ ከመናገር ወደ ኋላ አንልም። የአገሪቷ የፍትህ ስርዓቱ ተንኮታኩአል። እኔና ቤተሰቤ በአገሪቷ የፍትህ ስርዓት ክፉኛ ከተጎዱት ውስጥ አንዱ ነን። እኔ ደምበኛችሁ ሆኜአለሁ። እውነት ነው፣ ከእኛ በፊት የኦሮሞ ትንታግ ምሁራን ከእኛ በላይ ተጎደተዋል። ግን አሁንም ያ በደል በልጆቻቸው በእኛም ላይ ቀጥሎአል።
እኔ ምንም አይነት ወንጀል እንደሌለብኝ መቶ በመቶ አውቃለሁ። ከዚህ ቀደምም ሀሰተኛ መስካሪዎች ሀሰተኛ ስምና ማንነትነትን ተላብሰው አጠገቤ ቁጭ ብለው በሀሰት መስክረውብኝ ተፈርዶብኝ ነበር። ዛሬም ያንኑን እየደገሙ ነው። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ፣ እኔ በእውነተኛ ምስክር የተረጋገጠ ጥፋት ከተገኘብኝ ለመቀጣት ዝግጁ ነኝ። ደስም ይለኛል። ግን እየተካሄደብን ያለው ነገር እንደዚያ አይደለም።
በሚድያ እኛን ጭራቅ አድርጎ የማቅረብ ዘመቻ ቀጥሎበታል። ከዚሁ ዘመቻ የተነሳ እዚህ ያላችሁ ሰዎች ጭምር ስለ እኛ ምን አይነት አመለካከት እንዳላቸሁ ስጋት አለን።ስምና ምስሎቻችን የሌሉበት የለም: ዩቲዩብ፣ የህትመት ሚድያ፣ ማህበራዊ ሚድያዎች፣ ጋዜጦች ወዘተ የሌለበት የለም።
እኛ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሰርተን ጥሩ ኑሮ ለመኖር እድሉም ብቃቱም ያለን ሰዎች ነን። የአገራችን ጉዳይ ቢያሳስበን የህዝባችንን ችግር እንፍታ ብለን ነው እንጂ ወደ ትግሉ የገባን። የተከሰስንበት ወንጀሎች ሙሉ በሙሉ አልፈጸምንም። እንዲያውም እኔና ጀዋር በተቃራኒው እርቅን ለማውረድ የምንችለውን አድርገናል፤ የህዝቦች ግንኙነት ለመመለስ ብዙ ሰርተናል፤ ቤተክርስቲያንና መስጂድ የኛው ንብረቶች ናቸው፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጠብቁ ብለን አስተምረናል። ያለ በደላችን ነው የተወነጀልነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የበላይነትን ለመቀዳጀት እየተውተረተረ ያለ አካል እየታየ መጥቷል። እኛ እኩልነት ብቻ ብለን ነው እነዚህን የተቃወምናቸው። ለዚህም ከሌሎች ጭቁን ብሄሮች ጎን ቆመናል። ለምሳሌ የዎላይታ ህዝብ ህገ መንግስታዊ መብቱን በመጠየቁ ለትልቅ ጉዳት መዳረጉን ተቃውመናል። አሁንም እንዲህ አይነት ግንኘነታችን ይቀጥላል። እኩልነትና ፍትሀዊነት ብቻ ነው መፍትሄው። የበላይነትን የሚፈልግ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገው አካልን በመቃወማችን ነው ኢላማ ተደርጎብን የታሰርነው።
ሌላው ነገር፣ ደሞዝ የሚገባበት የሁሉም ቤተሰቤ የባንክ የሂሳብ ደብተር ታግዶብናል። እኛ በዘረፋ አልተከሰስንም፤ የባንክ የሂሳብ ደብተራችንን አግደውብን እያስራቡን ነው። አዝናለሁ። ቤተሰባችንን የማገድና የማንገላታት ዘመቻ ይቁምልን።
በመጨረሻም፣ ሀቀኛ ምስክር ይቅረብብንና እንቀጣለን፤ ጥፋተኞች መሆናችን በትክክል ከተረጋገጠ በሞታችንም ቢሆን ይህች አገር ሰላም ታገኝ። ሀቀኛ በሆነው ነገር ላይ ከፍርድ ቤቱና ከአቃቤ ህግ ጎን እንቆማለን።
(Source: Oromo Political Prisoners Defence Team)

No comments: