Friday, August 5, 2016

‪#‎EthioMuslims‬ ‪#‎EthioMuslimPeacefulStruggle

‪#‎EthioMuslims‬ ‪#‎EthioMuslimPeacefulStruggle‬
ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የተሰጠ መግለጫ
አርብ ሐምሌ 29/2008
የመግለጫው ሙሉ ቃል የፒዲኤፍ ሊንክ፡-
http://goo.gl/Cf0oMx
የመግለጫው ሙሉ ቃል በጽሑፍ እንደሚከተለው ቀርቧል...
***************
***************
ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› የተሰጠ መግለጫ
ፍትህ ዘር እና እምነት የማይገድበው የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ መብት ነው!
ለፍትህ ለሚደረግ ትግል የሰው ልጆች እጅ ለእጅ ሊያያዙ ይገባል!
አርብ ሐምሌ 29/2008
ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከአምስት ዓመታት በፊት ‹‹የእምነት ነጻነቴ ይከበር! ፍትህ እፈልጋለሁ!›› ብሎ በተነሳበት ወቅት አገራችን በፍርሀት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የነበረችበት ሁኔታ የሚዘነጋ አይደለም። መንግስት ምርጫ 97ን ተከትሎ በወሰደው እርምጃ ዜጎች እርስ በእርስ ተማምነው ጉዳያቸውን አደባባይ ማውጣት ቀርቶ ከበራቸው ጀርባ በአራት ግድድዳዎች መካከል ሆነውም እንኳን ደህንነት ተሰምቷቸው ችግሮቻቸውን ለራሳቸው ጆሮ ማድረስ የማይደፍሩበት ሁኔታ ሰፍኖ ነበር። ስርዓቱ ከዓመት ወደዓመት አምባገነን ባህሪውን እያሰፋ በመምጣት እና ለብዝሃይቱ አገራችን ምቹ የሆነውን የፌደራሊዝም ስርዓት በአፈጻጸም ጉድፎች በማበለሻሸት ህዝብ እርስ በእርሱ የማይተማመንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረጉ ዜጎች የብሄር ልዩነትን ተሻግረው በአንድነት ለመብታቸው ለመቆም ያልደፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ አንዱን ቡድን በሌላው የማስፈራራት ዘዴን በመጠቀምም ብዙ ችግሮችን ሲያስከትል ቆይቷል፡፡
እንግዲህ በእነዚህ ከላይ ባነሳናቸው ጉልህ እውነታዎች መካከል ነበር እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አገሪቱ ላይ ያጠላውን የፍርሀት ድባብ በመግፈፍ እና የዘር ልዩነት አጥርን በመሻገር ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ሶማሌ ወዘተ ተባብለን ሳንለያይ ባጠቃላይ ሁላችንም በቦታ፣ በጊዜ እና በሁኔታ ሳንገደብ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ድምጻችንን በአደባባይ ማሰማት የቻልነው።
በተለያዩ የሰለጠኑ አገራት ላይ ጭምር የሚሠራበትን ስኬታማ የፌደራል ስርዓት በአንባገነናዊ ባህሪው፣ በአፈጻጸሙ እና አካሄድ ስህተቶቹ እያበለሻሸ እና ለግል መጠቀሚያነት እያዋለ የዘለቀው ስርዓት የመብት ጥያቄያችንን ለማስጣል በወቅቱ የመዘዘው ካርድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ያነሳነውን የመብት ጥያቄ በክርስትያን ኢትዮጵያዊያን ላይ ያነጣጠረ፣ የአገሪቱን ደህንነት እና ጸጥታ የሚረብሽ፣ በውጭ ሃይሎች የሚዘወር እንደሆነ አድርጎ ለማሳየት መሞከር ነበር፡፡ አንዳችን በሌላኛችን ላይ ጦር ቀስረን እንድንነሳና ስርዓቱ የመሃል ዳኛ በመሆን ስልጣኑን እንዲያደላድል በማሰብ ብዙ ልፋት ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ ይህንን የመንግስት ሴራ ገና ከጅምሩ በመረዳት የጥያቄያችንን ይዘት እና የእንቅስቃሴያችንን ሰላማዊ መርሆች በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንደህዝብ ሆነን ማሳየት በመቻላችን ስርዓቱ እንደተመኘልን እርስ በርሳችን ወደመተላለቅ ሳይሆን ከመቸውም ጊዜ በላቀ መልኩ እርስ በእርስ ወደመቀራረብ መምጣት ችለናል - አልሐምዱሊላህ!
የሙስሊሙ የትግል ሂደት በዚሁ ከቀጠለ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም የራሴ ብለው ከያዙት ሊከተል የሚችለውን ጣጣ የተረዳው መንግስት ሌላ ስትራቴጂ ነድፎ በጥቅም ላይ ለማዋል ሞክሮም ነበር፡፡ ይኸውም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳው ጥያቄ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን የማይመለከት፣ ጉዳዬ ብለው ሊያዩት፣ ሊወያዩበት እና ሊመክሩበት የማይገባ፣ ጠባብ እና የጥቂቶች እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ነበር። በዚህም ዙሪያ እንቅስቃሴያችን የሙስሊሙ ጥያቄ በመሰረቱ በአገሪቱ ህገ መንግስት እና በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ቻርተር ላይ የሰፈረ እምነትን የመተግበር እና የመደራጀት መብት መሆኑን በማያዳግም መልኩ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ፍትህ፣ ነጻነት እና ከፍርሃት ነጻ የሆነ ህይወት የማግኘት መብት እምነት እና ዘር የማይገድበው መብት በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ለመንግስት ፕሮፓጋንዳ ደንታ ሳንሰጥ ለፍትህ መስፈን በአንድነት እንድንቆም እንደህዝብ ሆነን ጥሪ አቅርበናል፡፡ ውጤቱም የመንግስትን ሙስሊሙን ባይተዋር የማድረግ ሴራ ያመከነ እና አመርቂ ስኬትን ያስመዘገበ ነበር።
መንግስት በሴራ ስሌቱ እንደከዚህ ቀደሙ ስኬት አገኛለሁ ብሎ በእርግጠኝነት ተንቀሳቅሶ የነበረ ቢሆንም የሙስሊሙን ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ግን ለማምከን ሳይችል ቀርቷል፡፡ ግና ለማምከን ባደረገው ሙከራ የሰላም አምባሳደር የሆኑትን የእንቅስቃሴውን መሪዎች ማሰር እና ማስቃየት፣ ከዚያም አልፎ በፍርደ ገምድል ሂደት በሽብርተኝነት መፈረጅ ነበር፡፡ እንቅስቃሴያችን ግን ይህንንም መስዋእት እየከፈሉ ትግልን ማስኬድ፣ የበለጠ ጥልቅ እና ሰፊ ወደሆኑ ሂደቶችም ማሸጋገር እንደሚቻል በተግባር ማሳየት ችሏል።
አዎን! ሙስሊሙ ህብረተሰብ ድምጹን ማሰማት የጀመረው የተለያዩ የለውጥ አቀንቃኞች ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ስርዓቱን ሊደፍረው እንደማይችል ባመኑበት እና እንደ አማራጭም ከማየት በተሳነፉበት ወቅት ነበር። ግና ሰላማዊ ትግሉ ገዢው ስርዐት ከሰላማዊ መርሁ ለማስወጣት የደቀናቸውን መሰናክሎች እያለፈ በእርግጥም ሰላማዊ የትግል ሂደት ህዝቦችን ለማሰባሰብ እና በጋራ ለማስነሳት ትልቅ ሃይል መሆኑን በጽናት ማስመስከር ተሳክቶለታል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች አሁንም ቢሆን ከጅምሩ ያነሳናቸው ጥያቄዎች መልስ ባያገኙም ሙሉ መብታችንን በዘላቂነት ለማስከበር እና ብሄራዊ ጭቆናውን ለመግታት እያደረግነው ባለው ትግል ሂደት እንቅስቃሴያችን ፋና ወጊ ሆኖ የተጠቀመባቸው የትግል መርሆች እና ስልቶች በመላው ኢትዮጵያዊያን የመብት ትግል ውስጥ ጥቅም ላይ መዋላቸው በእጅጉ ያኮራናል፡፡ ትግላችን ለውዲቷ አገራችን እና ለህዝቦቿ ያበረከተው ልዩ አስተዋጾ እንደሆነም በኩራት እንድንናገር ያደርገናል።
ምንጊዜም ቢሆን ትግላችን ከግብ ለማድረስ የጀመረውን የትግል ሂደት አጠናክሮ እያካሄደ በነበረበት ወቅት ሁሉ በአገራችን ለፍትህ፣ ለነጻነት እና ለዲሞክራሲ ግንባታ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያለበትን ሃላፊነት ከመወጣት የተዘናጋበት ሁኔታ የለም። በቀጣይም እምነታችን የግላችን፣ አገራችንን የሚመለከቱ ጉዳዮች ደግሞ የጋራችን በመሆናቸው ለትግላችን መነሻ የሆኑ መሰረታዊ የእምነት ነጻነቶቻችንን ጨምሮ ሌሎች የዜግነት መብቶቻችንን በዘላቂነት በማስከበሩ ሂደት ተሳትፏችንን አሳድገን ልንቀጥል ይገባል፡፡ በዚህ ሂደትም እስላማዊ እሴቶቻችንን በማስጠበቅ በኩል ያለብንን ሃላፊነት ሳንዘነጋ እና እስላማዊ እሴቶቻችንን እና ሀይማኖታዊ ግዴታዎቻችንን ሳንጥስ በአገራዊ ጉዳዮች እና እንቅስቃሴዎች ላይ እስካሁን እያደረግን ያለውን ተሳትፎ አሳድገን እና አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የዜጎችን ድምጽ በፕሮፓጋንዳ እና በአፈሙዝ ዘላለም አፍኖ መያዝ እንደማይቻል ስርዓቱ ዛሬም ላይ እንኳ ቢሆን ሊረዳ ይገባል፡፡ የሙስሊሙን ጥያቄዎች ከመመለስ እና በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ እስረኞቻችንን በነጻ ከማሰናበት ጀምሮም ኢትዮጵያዊያን ለሚያነሷቸው የፍትህ እና የነጻነት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት የጥፋት ታሪኩን ሊያድስ ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአጓጉል እምቢተኝነት የሚቀጥል ከሆነ ግን በታሪክም ከተወቃሽነት እንደማይተርፍ ተረድቶ አገሪቱን ከጥፋት ይታደግ ዘንድ እናሳስባለን!
ሰላማዊ የትግል መርሃችን እና አንድነታችን ምንጊዜም የማንጥሳቸው ጽኑ መሰረቶቻችን ናቸው!
ለፍትህ እና ፍትሃዊነት፣ ለነጻነት እና ለእኩልነት የሚደረግ ትግል ምርጫችን ሳይሆን ግደታችንም ነው!!!
ፍትህ ለፍትህ ፈላጊዎች ሁሉ!!!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
Like  Comment  Share 

No comments: