Tuesday, July 21, 2020

#AbiyMustGo#Ethiopia

አብይ ለስንተኛ ጊዜ ባለፈው ሳምንትም ኤርትራን ጎብኝቷል። ጉዞው የሁለት አመቱን ጉዞ ለመገምገም ነው የተባለው ግን ቀልድ ነው። ምንም የሚገመገም ነገር የለም። 
---
የጉዞው አንደኛው ምክንያት ከሻእቢያ ጋር ህብረት በማድረግ የትግራይ ህዝብ ለብልጥግና እጅ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። በተለይ የክልሉ መንግስት ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱና የምርጫ አስፈፃሚ መምረጡ አብይን እረፍት እንደሚነሳው አያጠራጥርም። ዝም እንዳይል ጥርስ አልባ አንበሳ መሆኑ ይጋለጣል። ጦርነት እንዳይጀመር መጨረስ እንደ መጀመር ቀላል አይሆንም። ፓርቲውም ቢሆን ሊነግሩን እንደሚሞክሩት ጠንካራ cohesion የለውም። በኦሮሚያ ከዚህ በፊት ጥያቄ ካነሱት በተጨማሪ በርካታ ካድሬዎች በተለይ በነዚህ ሶስት ሳምንታት ገሃድ የወጣ አሀዳዊ መንግስት እያገለገሉ መሆኑን ተረድተዋል። የደቡብ ክልል አመራሮችም የጠቅላዩ አሃዳዊ እይታና ጥሩ ኢትዮጵያዊነትን እግሬ ስር ተቀምጣችሁ ተማሩ ማለት ፈፅሞ እንደማይስማማቸው ይታወቃል። ራስን ለማስተዳደር የሚያነሱትን ጥያቄ እጅግ simplistic በሆነ መንገድ V8 ለመንዳት የሚደረግ እሽቅድድም ብሎ ደጋግሞ ወርፏቸዋል። በአማራ ክልል ለጊዜው ድጋፍ ያገኘ ቢመስልም ያ የሚቀጥለው የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ምሁራንን ቀርጥፎ እስከበላላቸው ድረስ ብቻ ነው። ከዛ በኋላ እንደሚነሱበት ጥርጥር የለውም። ለዶ/ር አምባቸውና ለምግባሩ ያልሆነ ክልል ለኦህዴዱ አብይ ይሆናል ማለት መቼም ፌዝ ነው። ለጊዜው በአሃዳዊ ህልም ከነሆለለና ለዝርፊያ ከተደራጀ urbanite ውጪ ምንም ማህበራዊ መሰረት የሌለው አብይ ጦርነት ጀምሮ የማገባደድ አቅም የለውም። በመሆኑም ከውጪ ሃይል ጋር በትብብር የገዛ ሀገሩን ህዝብ በወታደራዊ ሃይል የመጨፍለቅ ህልም አለው።  በዚህም መሰረት የኤርትራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ሳዋን በመጎብኘት የመጀመሪያው መሪ ሆኗል። የለየለት አምባገነን ሆኖ ለመግዛት አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን እየቀሰመም ተግባራዊ እያደረገም ነው። ሆኖም ከትግራይ ጋር ያለውን ልዩነት በዚህ መልክ መፍታት ቀላል አይሆንም። የሌላውን ክልል ህዝብም በወታደራዊ ሃይል በቋሚነት እገዛለሁ ማለት ቂልነት ነው። የት ድረስ እንደሚያስኬደው የምናየው ይሆናል። 
---
ሌላኛው የጉዞው ምክንያት ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር ላይ የአሸማጋይነት ሃላፊነት የወሰደው ኢሳያስ የሚለውን ለመስማት ነው። ከሁለት አመታት በፊት ተደማጭነት የሌላት pariah state የነበረችው ኤርትራ ዛሬ በግድቡና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ major power broker እንደሆነች እየተዘገበ ነው። ኢሳያስ በቀጠናው ላይ ተሰሚነቱን ለመጨመር ግድቡ ላይ አይኑን ጥሏል። ውስብስብ ዲፕሎማሲ ላይ እምብዛም ለሆነው አብይ ኢሳያስ ድርድሩን በውክልና እያካሄደለት ነው ቢባልም ማጋነን አይሆንም። በነገራችን ላይ ለበርካታ ወራት ግድቡን እንሞላዋለን ሲባል የነበረው ከሰማይ በቀጥታ ቋቱ ውስጥ በሚዘንብ ዝናብ ነበር እንዴ? እንሞላዋለን ከተባለ ሶስት ሳምንት ቢያልፈውም  አንዴ ጀምረናል አንዴ አልጀመርንም አንዴ በተፈጥሯዊ መንገድ ማለታችን ነው የሚል ማደናገሪያ እየተለቀቀ ነው። ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የማይችለው መንግስት ጠንካራ ጥያቄ ይጠይቃሉ ብሎ ያሰባቸውን ፖለቲከኞች አስቀድሞ ሰብስቦ በማሰር ከተጠያቂነት አምልጧል። 
---
ለማንኛውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ወሳኝ ምእራፍ ተሸጋግሯል። በበርካታ ክልሎች ቅቡልነቱ የወረደው አብይ ከእንግዲህ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሃይልን ተጠቅሞ የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ ስርአት መዘርጋት ነው ብሎ ያምናል። ከዚህ በፊት "ምርጫ የማያደርጉ ሀገራት አሉ። ምርጫ ማድረግ ግዴታ አይደለም" ብሎ እንደነገረን ከእግዲህ የምርጫን ጉዳይ ያነሳል ተብሎ አይጠበቅም። እንኳን ሀገራዊ ምርጫ በፓርቲ ደረጃ ጉባኤ ለማድረግና የብልጥግናን ፕሬዚደንትና ምክትል ለመምረጥ እስካሁን ምንም ፍላጎት የለውም። በሚስጥራዊ ድምፅ አሰጣጥ የጉባኤ ምርጫ ቢካሄድ ከሚጠበቀው እጅግ ያነሰ ድምፅ እንደሚያገኝ በሚገባ ያውቃል። በዚህም ምክንያት በቅድሚያ በሚደረግ ግምገማ ብዙ ሰዎችን ከፓርቲው ማራገፍና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በሀሰት ክስ እንዳሰረው ሁሉ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን የራሱ ፓርቲ አመራሮች ማሰርና ማስወገድ የመጨረሻው እርምጃ ይሆናል። ሌሎች ተቀናቃኞች ቢወገዱ እንኳን በሶስት መሪዎች ስር ምክትል ሆኖ የሰራው ደመቀ መኮንንም (ስለሺ ስህን) የፓርቲ ፕሬዚደንትነቱን ቦታ መመኘቱ open secret ነው። የጊዜ ጉዳይ ነው። መናከስ ይጀመራል። አሁን መንግስትም ሆነ ፓርቲ የሚባል ነገር የለም። ያለው ግለሰብ ነው። አንድ ፈላጭ ቆራጭ ሁሉን በያኝ ግለሰብ። ሌላው ሳያወላዳ ትእዛዝ መፈፀም ብቻ ነው። ነገ ወደ አዳማ የሚያመራው ንጉሱ ጥላሁን አንድ ውይይት ላይ ለምን ጉዳይ ነው የምትሄደው ሲባል ስደርስ ነው የሚነገረኝ እንዳለው ማለት ነው። አብይ ይህ አምባገነናዊ ጉዞው መጨረሻ ላይ እንደሚከሽፍ እርግጥ ነው። ጥያቄው በዚህ ሂደት ሀገሪቱስ ትተርፋለች ወይስ አስቀድመን እንሰናበታት ነው።

No comments: